Wednesday, June 3, 2009

በዋሺንግተን ዲሲ የተከበረው የግንቦት 20 የድል በዓል።

ከዋሸራ_2
ግንቦት 22፣ 2001 ዓ.ም.

መታደል ሆነና በዕለቱ ዕረፍት ላይ ስለነበረኩኝ፣ በዓሉ ወደሚከበርበት ሥፍራ ወደ ኢትዮጵያ ኤንባሲ አመራሁ። እኔ እንኳን ከከተማ ራቅ ብዬ ስለነበር የምመጣው ትንሽ ዘግይቼ ነበር የደረስኩት። ሌሎች ተጋባዦችም ልምድ ሆነና ትንሽ ዘግየት (ብዙ ዘግየት!) ብለው ደረሱ። ይሄንን ዘግይቶ የመድረስ ጉዳይ አንድ ቀን ክነፉን ሰብረን መጣል ይኖርብናል። ለዛሬ ግን በዓሉ ላይ ላተኩር።

ታዲያ አዳራሹ እንደሞላ፣ እንግዶቹን በደመቀና በሚያኮራ ንግግር የከፈቱት ያንባሳደሩ ምክትል የሆኑት አቶ ወንድሙ አሳምነው ነበሩ። እውነትም እንኳን መጣሁ የሚያሰኝ፣ የበዓሉን ስብዕናና ተገቢ ትርጉም ያዘለ ንግግር ነበር ያደረጉት። የዕለቱን የክብር እንግዳ ክቡር አቶ ስብሃት ነጋን፣ "እያከበርን ያለውን ቀን እውን ለማድረግ በተኪያሄደው እልህ-አስጨራሽ የትጥቅ ትግል ከጀመሩትና ከመሩት ቁልፍ ሰዎች አንዱ" መሆናቸውን ካስገነዘቡን በሗላ ያደረጉት ንግግር፣ አንድም መሬት ጠብ የሚል አልነበረም።

"የግንቦት 20 በዓልን ስናከብር፣ ለዚች ቀን የተከፈለውን መስዋእትነት ማስታወሳችን አይቀርም። ይህችን ቀን ለማምጣት፣ ህይወትን ገና ያላጣጣሙ ለጋ ወጣቶች ተቀጥፈዋል። ወላጆች የሞቀ ቤታቸው ፈርሶ የወላድ መሃን ሆነዋል። በአሰርት ሺዎች የሚቆጠሩ ጀግኖች የድሎት ህይወትን ንቀው፣ የወጣትንት ዘመናቸውን በበረሀ አሳልፈዋል። በዚች ቀን እነዚህን ጀግኖች እናስታውሳቸዋልን። በዚች ቀን፣ በከባድ መስዋእትነትና ድካም የፈሰሰውን የጨለማ ዘመን በማንኛውም መልኩ እነዳያንሰራራ የበኩላችንን ለመስራት ቃላችንን እናድሳልን።"

የጀመርኩትን የዲር ፓረክ ውሃ ቁጭ አድርጌ የሞቀ ጭብጨባ የጀመርኩት ብቻዬን አልነበርም። አዳራሹ ውስጥ የተሰበሰቡት ከ250 በላይ የሚሆኑት እንግዶች በሙሉ ባነድነት አጀቡኝ።
አቶ ወንድሙ ቀጥለውም፤

"ግንቦት 20 ልዩ ትርጉም የሚሰጠን የደርገ ስርዓትን ማፍረሱ ተልዕኮ በድል የተጠናቀቀበት እለት በመሆኑ ብቻ አይደለም። ግንቦት 20 የምናከብረው ማንኛውም አይነት ያድልኦ ስርአት በአገራችን ዳግም እንዳይመለስ፣ ኢትዮጵያን በአዲስ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ስርዓት ላይ መገንባት የጀመርንብት ቀን በመሆኑ ጭምር ነው።

በህብረተሰባዊ ስርዓት ለውጥ ሂደት የአዲስ ስርዓት ግንባታ ምዕራፍ አስቸጋሪው ምዕራፍ ነው። ብዙ አገሮች አሮጌውን ማፍረስ ቢችሉም፣ አዲሱን መገንባት ተስኗቸው፣ ወደ ሗላ ሲንሸራተቱ እያስተዋልን ነው።

በኤርትራ፣ በሶማሊያ፣ በኮነጎ፣ በኢራቅ፣ በአፍጋኒስታን፣ ወዘተ... የምናያቸው የድህረ-ስርዓት ማፍረስ ትርምሶች፣ የግንባታውን ሂደት አስቸጋሪነት የሚያሳዩ ናቸው። በድህረ ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ሁኔታ ከዚሁ በመሰረቱ የተለየ ነው። ኢህአዴግ ማፍረስ ብቻ ሳይሆን መገንባትም ጭምር ችሎበታል። ለዚህም ነው አገራችን በተተረማመሰ አካባቢ የልማት፣ የዲሞከራሲና የሰላም ደሴት የሆነችው።"

እንዲህ ነው እንጂ ያገሬ ልጅ! አቶ ወንድሙ፣ ምናልባትም ወደ ሰላሳዎቹ መጨረሻ ወይንም ወደ አርባዎቹ መጀመሪያ ገደማ ዕድሜ ያላቸው ብሩህ ጎልማሳ ናቸው። ንግግራቸውን በሚያደርጉበት ጊዜ ፊታቸው ላይ የሚነበበው ገፅታ በስሜትና በወኔ የተሞላ ነበር። ከዛሬ ሃያ ዓመት በፊት የተሰዉትን ወጣቶች ሲጠቅሱ፣ በዛ ዕድሜ እሳቸው የት እንደነበሩ ሁሉ እያስታወሱ መሆኑ በግልጽ ይታይባቸው ነበር። ይህን እነባ-አነቅ ንግግራቸውንም በመቀጠል፤

"በአሁኑ ወቅት አገራችን በአጠቃላይ ለውጥ ላይ ነች። አንዳንድ ታዛቢዎች በ80ዎቹ መጀመሪያ የነበረችው ቻይና ትመስላለች ይላሉ። ለውጡ፣ በበርካታ ታዳጊ አገሮች እንደሚታየው የመቀባባት ለውጥ አይደለም። በተወሰኑ ከተሞች የሚታይ የብልጭልጭ ለውጥ አይደለም። በጠቅላላ የአገሪቱ 80 ሚሊዮን ህይወት ከመሰረቱ እየቀየረ ያለ ለውጥ ነው።

ሚሊዮኔር ገበሬዎች ማየት ጀምረናል። ለዘመናት በማያቋርጥ እንቅልፍ ውስጥ የነበሩት ገጠሮች ህይወት እየዘሩ ናቸው። መብራት፣ ስልክ፣ መንገድ በየዳር አገሩ እየገባ ነው። ከ95% በላይ የገጠር ልጆቻችን ት/ቤት ገብተዋል። እአንዳነዱ የገጠር ቀበሌ፣ በሚያዳርስ መልኩ ከ45,000 በላይ የእርሻ ባለሙያዎች ተሰማርተው፣ ዘመናዊ እርሻና ዘመናዊ ህይወት ገበሬአችንን እያስተማሩት ነው። በእያንዳነዱ የገጠር ቀበሌ የተሰራጩት፣ ከ30,000 በላይ የሚሆኑ የጤና ባለሙያዎች፣ ቁስሉን እያከሙለት ነው። በተወሰኑ የጤና ጥንቃቄና የመከላከያ ዘዴ፣ ለዘመናት የገጠሩን ህዝበ ሲፈጁ የነበሩ በሽታዎች እየጠፉ ናቸው።

ህዝባችን፣ በሰለጠነው ዓለም ከሚገኙ የፓልቶክ አርበኞች በተሻለ መልኩ፣ የዴሞከራሲ ባህሉን እየገነባ ይገኛል። በኢትዮጵያ በህዝበ-ይሁንታ ከተመረጠ መስተዳድር ውጭ ምንም አይነት በእናውቅልሃለን ሽፋን የሚመጣ የጭቆና ስርአት የማይታሰብባት ደረጃ ላይ ደርሰናል። በውስጥ ጥንካሬአችንም ምክንያት፣ በዓለም-አቀፍና በአህጉራዊ ፖለቲካ ያለን ቦታ፣ ከምንም ጊዜ በላይ እየደመቀ መጥቷል። በአጭሩ፣ የኢትዮጵያ ትንሳኤ ከመፈክር በላይ ሆኖአል። የኢትዮጵያ ትንሳኤ የሚጨበጥ እውነታ እየሆን መጥቷል።"

እነዲህ እያሉ ነበር እንግዲህ አኩሪአችን፣ አቶ ወንድሙ ንግግራቸውን ወደ መደምደሚያው ያሻገሩት። አዎን ከውሃውም ተጎንጭተናል፣ ከቁም-ነገሩም ትንሽ ቀስመናል። ታዲያ ፕሮገራሙ ገና መጀመሩ ነበር።

"እዚህ ልናስታውሰው የሚገባ ቁምነገር፣ የሂደታችን ስኬት በአጋጣሚ የመጣ አለመሆኑ ነው። ስኬቱ የመጣው ያገራችን ችግሮች ቀላሎች ስለሆኑ አይደልም። ለነገሩ፣ የተጀመረውን ለውጥ ለማጨናገፍ ከውስጥና ከውጭ የተወጠኑት ሴራዎች ብቻ ሳይሆኑ ፣ የወረስነው ውስብስብ የፖለቲካ ችግር፣ ለዴሞከራሲ ባዕድ የሆነው የፖለቲካ ባህላችንና የደቀቀውና የተራቆተው ኢኮኖሚ፣ ሂደቱን የበለጠ እንዲወሳሰብ ያደርጉ ነበሩ።

የስኬታችን ዋነኛ ሚስጥር፣ መንግስት የአገሪቱን ቁልፍ ችግር ለይቶ፣ እነዚህን ችግሮች በተስተካከለ ፖሊሲና ስትራቴጂ መፍታት በመቻሉና በየወቅትዩ እንደ እሸን የሚፈሉትን ችግሮች፣ ያስቀመጠውን የመጨረሻ ግብ፣ በማያዛባ መልኩ በማስተዋል መፍታት ስለቻለ ነው።

ይህ ሲባል፣ በዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ችግር የለም ማለት አይደለም። ከጅምሩም የ3,000 ዘመን ችግር በሀያ ዓመት እንፈታልን ብልን አልጀመርንም። የክርክራችን ነጥብ፣ ችግሮች አሉ ወይስ የሉም የሚለው ሊሆን አይችልም። ውይይታችን ችግራችንን በሚፈለገውና በሚቻለው ፍጥነት እየፈታን ነው ወይ? እያንዳንዳችንስ ለመፍትሄው ምን አስተዋፅኦ አድርገናል? ወይስ እያደረግን ነው ወይ? የሚለው መሆን ይኖርበታል። ችግሮቻችንን በዚሁ መልኩ ከተጋፈጥናቸው፣ አለምንም ጥርጥር ወደ መፍትሄዎቻችን በቶሎ እንደርሳልን።


በኢትዮጵያ አሁን ያለው ለውጥ፣ እንደ ክረምት ጎረፍ መመሰል ይችላል። ማንም ሊያቆመው አይችልም። የዚህ ጎርፍ ፍጥነት እንዳይቀንስ፣ የየበኩላችንን እናድርግ።"

ሌሎች ተናጋሪዎችና ግብዣው ለሰዓታት ቀጠለ። የአቶ ወንድሙ ንግግር ግን፣ የነገዋ ኢትዮጵያ በጥሩ እጅ መሆኗን አስረግጦ አለፈ። እኔም ደስታ በተሞላው መንፈስ ወደ ቤቴ አመራሁ።

No comments: