Tuesday, February 2, 2010

ከፍርሃት ነፃ መውጣት

ከፊልስ ከርክ
ትርጉም - ከዋሸራ
Sunday, January 17, 2010


በዘመናችን የሰው ልጅ ዕድሜ ሰባ-አምስት ዓመት ገደማ ነው ብለን ብንቀበል በቅርቡ ሲሶውን ዕድሜዬን አገባድጄዋለሁ ማለት ነው። ሆን ብዬ ያለፈውን ህይወቴን ስቃኘውና ስመረምረው ብዙ አዳዲስ ግኝቶች ታይተውኛል። ብዙዎቹ ተስፋ ሰጪና የሚያስደስቱም ናቸው። በጣም የሚያስደነግጠው ነገር ግን የመጀመሪያውን የህይወቴን ክፍል በሙሉ ፍራቻ ማሳለፌና የተረፈውን ጊዜ ደግሞ እነዛን ፍራቻዎቼን ከሰው የምደብቅበትን ብልሃትና ጥበብ ስማርና ሳጠና ማሳለፌ ነው። የዚህ ድርጊቴ አሳዛኙ ክፍል፣ አለመፍራቴን ለሰዎች ለማሳወቅ የወሰድኩት የድለላ ተግባር መልሶ እራሴን መደለሉ ነው።

ፍርሃት በህይወቴ ውስጥ ያሳደረውን ትልቅ ተጽዕኖ ድንገት በተገነዘብኩበት ጊዜ ይህ ነው የማይባል ድንጋጤ አደረብኝ። ምክንያቱም ለህይወት ያለኝ ፍቅር መጠን የሌለውና ህይወትን ለመኖር የሚያስፈልጉትን ሙከራዎች በሙሉ ስራ ላይ የማዋል የፀና እምነት ስላለኝ ነው። ለፍርሃት በምናጎበድድበት ጊዜ የግላችንን ኑሮ ያለፍርሃት በመኖር የምናበርክተውን የሰውን ልጅ ህይወት ትርጉምና ዋጋ የመስጠት ሃላፊነት እንገድበዋልን የሚል የጠበቀ እምነትም አለኝ። በህይወት ኑሮአችን ጊዜ ለራሳችን ብቻ ሳይሆን ለርስበርሳችንም ጭምር ትልቅ ሃላፊነት አለብን ብዬ አምናለሁ።

ፍርሃት አለመቻቻልንና አግባብ የሌለው ጥላቻን እንድንፈጽም ከማድረጉ ባሻገር በጣም የሚያሳዝነውና እንደ ከባድ ወንጀል ሊቆጠር የሚገባው ድርጊቱ ለውጥን የመቀበል ችሎታችንን የመስበር ሀይሉ ነው ብዬ አምናለሁ። ፍርሃት የለውጥን ተፈጥሮአዊነትና ለውጥ የዕውቀትና የዕድገት ፍሬ መሆኑን እንድንዘነጋ ያደርገናል። የለመድነውና የማያሰጋ የሚመስለን ነገር ላይ እንድንጣበቅ ይገፋፋናል። በአንድ ዳሰሳ የማናውቀውን እንድንጎዳና ፍርደ-ገምድል እንድንሆን ይጋብዘናል። በፍርሀት ወጥመድ ውስጥ ሆነን የውጭን ፍቅር ለራሳችን ብቻ ስናሳድድ ውስጣችን ያለውን ፍቅር እንድንረሳ ያደርገናል።

በመፍራት የሃይማኖት ቤታችንን በር እንዘጋለን የአባሎቻችንንም መጠን እንወስናል። የምናውቀውን ዜማ ለማዜም ፈቃደኛ የሆነውን ሰው እንጠጋለን። የራስን ችግር አውቆና እምነትን በማጠናከር ጥሩ ምግባርን የበላይነት ቦታ ከሚሰጥ ይልቅ የምናመልክበትን ስርዓትና የአምላኪውን አምላክ ስም የበለጠ ከብሬታ እንሰጠዋለን።

በልጅነታችን የወላጆቻችንን ራዕየ-ቢስ የሆነ አግባብ የሌለው ስርዓት እንድንናውቅ እንደረጋለን። እኛም በተራችን ለልጆቻችን ይሄንኑ ወይም ይሄንኑ መሰል በፍርሃት የተመሰረተና የታጠረ ስርዓት እናስተምራቸዋለን። እኔ የማይፈራ የራሴ የሆነ ልጅ እፈልጋለሁ። የሱ ከፍርሃት ነፃ መሆን ግን ከኔ ይጀምራል ብዬ አምናለሁ። ምክንያቱም የግሌን ህይወት ያለፍርሃት በመኖር ለህይወት በሙሉ ያለኝን ሃላፊነት እወጣዋለሁ የሚል ፅኑ ዕምነት ስላለኝ ጭምር ነው። ልጁ ውስጤ ገና ስላልተጸነሰ የትላንትናውን ስህተት ለመቐቐም ዛሬ በቂ ዕድገት ማሳየት አለብኝ ብዬ አምናለሁ።

ነገ ተስፋ ያለው ቀን መሆኑንም አምናለሁ። ነገ ይህንን ዓይነት ተስፋ ካለው ከዛሬ የተለየ በመሆኑ ነገን መፍራት የለብኝም። በማውቀውም ሆነ መፍራት በሌለብኝ በማላውቀው ነገር ሁሉ ዳግመኛ ላለመፍራት ትልቅ ጥረት ማድረግ እንዳለብኝ አምናለሁ። ሁላችንም ጥፋት አጥፍተናል፤ ሁላችንም ብቸኛ ነን። ጥፋተኛም ሆንን ብቸኛ ሁላችንም በዚች ዓለም ላይ አብረን ነዋሪዎች ነን።

No comments: